ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የንግድ ፈቃድ ማውጣት የሚቻለው በበይነ መረብ ብቻ መሆኑን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር የተጀመረው በበይነ መረብ የንግድ ፈቃድና ምዝገባ የመስጠት አገልግሎት፣ ኅብረተሰቡ በታሰበው ልክ እየተጠቀመበት
እንዳልሆነ፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ጅራታ ነመራ ገልጸዋል።
የንግድ ሥርዓቱን ቀላል ለማድረግ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል አገልግሎቶችን በበይነ መረብ ማድረግ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ
ጅራታ፣ ለዚህም ከሐምሌ ወር ጀምሮ ንግድ ቢሮዎች በአካል በመገኘት የሚደረገው ምዝገባና የፈቃድ አሰጣጥ ሙሉ ለሙሉ ይቀራል ብለዋል።
አሠራሩ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚወስደውን ጊዜና ገንዘብ ከመቀነስ ባለፈ መደበኛ የንግድ ሥራን ለማበረታታት፣ ሙስናን ለመከላከል፣ በንግድና ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የንግድ ፈቃድና ምዝገባውን ለማድረግ ከዚህ በፊት ሲጠየቅ የነበረው የቤት ኪራይ ውልም የማያስፈልግ በመሆኑ፣ ተገልጋዮች በቀላሉ መመዝገብና ፈቃድ መውሰድ ይችላሉ ብለዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶር) በበኩላቸው፣ በበይነ መረብ ንግድ የሚያከናውኑ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመርያ ተዘጋጅቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡንና በቀጣይ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል ብለዋል።
መመርያው ሲፀድቅ ሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ምዝገባ በማድረግ ምዝገባ ያላደረጉትን መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል። ፈቃድ ሳያወጡ
የሚሠሩትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አድራሻቸውን በመከተል ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው አብዮት (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የበይነ መረብ ንግድ አዋጁ ሰዎች የግል ንብረታቸውን በበይነ መረብ መሸጥ እንደሚፈቅድ ጠቅሰው፣ ሽያጭ ሲያከናውኑም ተገቢውን ታክስ መክፈል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።