Export Products

በ2014 በጀት ዓመት በመጀመርያው ግማሽ ዓመት ከአበባ፣ ከአትክልትና ከፍራፍሬ የወጪ ንግድ ከ286.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱና 20 በመቶ መጨመሩ ተገለጸ፡፡

ከአበባ፣ ከአትክልና ከፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በበጀት ዓመቱ በመጀመርያው ግማሽ ዓመት ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የነበረው 269.01 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ሆኖም አፈጻጸሙ ከዕቅድ በላይ 112 በመቶ ማሳካት መቻሉን፣ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ20 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ያመለክታል፡፡ በዚህ ዘርፍ በስድስት ወራት ውስጥ ከአበባ 246.4 ሚሊየን ዶላር፣ ከአትክልት 31.09 ሚሊዮን ዶላርና ከፍራፍሬ ደግሞ 9.04 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም ይኼው የማኅበሩ መረጃ አመልክቷል፡፡

የአበባ የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንፃር 106 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፣ ከዓምና ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ ደግሞ ግኝቱ በ16 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡ ወደ ውጭ የተላከው የአበባ መጠንም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ15.8 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአትክልት የወጪ ንግድ በተለይ ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡ በግማሽ ዓመቱ 75,774 ቶን አትክልት ተልኮ 27.6 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ 98.958 ቶን መላክ ተችሎ 31.09 ሚሊዮን ዶላር ሊገኝ መቻሉን አመልክቷል፡፡ ይህም በመጠን የዕቅዱን 131 በመቶ ሲያሳካ በገቢ ደረጃ ደግሞ አፈጻጸሙ 113 በመቶ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ከገቢ አንፃር ደግሞ ከአትክልት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀዳሚው ዓመት የ65 በመቶ ብልጫ የታየበት እንደሆነም፣ ተገልጿል፡፡ ወደ ውጭ የተላከው አትክልት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የመጠን ጭማሪውም 48.4 በመቶ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የፍራፍሬ የወጪ ንግድ አፈጻጸሙንም በተመለከተ የማኅበሩ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በመጀመርያው ስድስት ወራት 22,334 ቶን ተልኮ 9.04 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ነበር፡፡ አፈጻጸሙም ከመጠን አንፃር 95 በመቶ ማሳካት መቻሉ በመረጃው ተገልጿል፡፡ በገቢ ደረጃ ደግሞ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ያህል 9.04 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ ያሳያል፡፡

የፍራፍሬ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ደግሞ በገቢ ደረጃ የ22 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በአጠቃላይ ከሆልቲካልቸር ዘርፍ በግማሽ ዓመት 154,918 ቶን አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለመላክ ታቅዶ የተላከው ግን ከዕቅድ በላይ 174,252 ቶን መላክ ተችሏል፡፡ ይህም አፈጻጸሙ 107 በመቶ ሲሆን፣ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው የ2013 የመጀመርው ስድስት ወራት አንፃር ሲታይ የውጭ ምንዛሪ ግንቱ በ20 በመቶ በመጠን ደግሞ የ33.2 በመቶ ዕድገት መታየቱን ነው፡፡

በቀዳሚው ዓመት የመጀመርያው ስድስት ወራት የተላከው የአበባ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት መጠን 130,790 ቶን ሲሆን፣ ያስገኘውም የውጭ ምንዛሪ 239.6 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይኼው መረጃ ያመለክታል፡፡  

Published on 30 January 2022 ዳዊት ታዬ - ሪፖርተር ቢዝነስ 

Gmail

Related Post