petroleum fuel
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ከዓለም አቀፉ የገበያ ሥርዓት ተነጥሎ በራሱ እንዳይቆም ከሚያስገድዱት አንዱ ነዳጅ ነው፡፡ በማዳበሪያ፣ ድንጋይ ከሰልና ብረት በቅርቡ ራሳችንን እንችላለን ብለው የተነሱት የማዕድን ሚኒስትሩ እንኳን ኢትዮጵያ በነዳጅ ራሷን ትችላለች ለማለት አልደፈሩም፡፡

በዓለም አቀፉ ገበያና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ልዩነት ለማጥበብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ያፀደቃቸው መመርያዎች ግን ነዳጅ በኢትዮጵያ ሸማቾች ላይ የሚያደርሰው ጫና እየገዘፈ እንደሚሄድ ጠቋሚ ናቸው፡፡

‹‹በሊትር እስከ ሃያ ብር እየደጎምኩ ሳቀርብ ነበር›› ያለው መንግሥት በቅርቡ ግን የአገር ውስጥ ዋጋዎቹን ከዓለም ጋር ለማስተካከል ወስኗል፡፡ በ2013 መንግሥት ወደ 25 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጌያለሁ ቢልም፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ነዳጅ ዋጋ ከበርሜሉ ዋጋ በታች በወረደበት ሰዓት በገፍ ገዝቶ ማከማቸት ግን አልተቻለም፡፡

አዲሱ መመርያ የግሉ ዘርፍ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሙሉ የነዳጅ ዋጋውን መሸከም እንዲጀምር የሚያዝ ሲሆን፣ ለመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ግን ድጎማው ቀስ በቀስ እየተነሳ በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲያልቅ ወስኗል፡፡

ይኼ ማለት ድጎማው ለግሉ ዘርፍ በየሦስት ወሩ 25 በመቶ እየተነሳ በአንድ ዓመት ያልቃል፡፡ ለመንግሥት ዘርፍ ግን አሥር በመቶ በየስድስት ወሩ እየተነሳ በአምስት ዓመት ያልቃል፡፡

ድጎማው ሲነሳ ለግሉ ዘርፍ ነዳጅ ከዓመት በኋላ በሊትር 50 ብር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም አሁን ካለበት 30 ብር አካባቢ በዓመት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እያወጣች ወደ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ውጤቶችን ታስመጣለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ናፍጣ ሲሆን፣ በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ተፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የግንባታ ማሽነሪዎች፣ ጄኔሬተር የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በድጎማው መነሳት ተጎጂ ላለመሆን አዳዲስ የዋጋ ማስተካከያዎችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

የመመርያዎቹ አንዱ ዓላማ በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በኤክሳይስ ታክስ ተሞክሮ ያልተሳካውን የተሽከርካሪዎች ብዛት ለማመጣጠን የታለመ ነው፡፡ መንግሥት ወደ ሕዝብ ትራንስፖርት ሲያደላ ትናንሽ መኪኖች ግን ዋጋቸው ሰማይ ነክቶ እንኳ ከመግዛት የሚቦዝን አልተገኘም፡፡

በአገሪቱ ካሉት ወደ 1.2 ሚሊዮን መኪኖች በሕዝብ ትራንስፖርት ውስጥ የተሰማሩት 300,000 አካባቢ ናቸው፡፡ በእርግጥ ወደ 600,000 መኪና የሚጋፋባት ርዕሰ መዲናዋ 150 ነዳጅ ማደያዎች ብቻ ይዛ የተመጣጠነ የነዳጅ ክፍፍል ማሰብም ሌላው ራስ ምታት ሆኖ የቀጠለ ችግር ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፉ የነዳጅ ገበያ አንድ በርሜል ዋጋ በአጭር ጊዜ ተፈትልኮ ሰማንያ ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ በቅርቡ መቶ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሦስት ከመቶ የሚሆነው ቤተሰብ የነዳጅ ውጤቶችን ለማብሰያ የሚጠቀም ሲሆን፣ ከግሉ ዘርፍ ቀጥሎ ተጎጂ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

አጥናፉ ገብረ መስቀል (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዋጋ ንረት (Inflation) አስተማሪና ተመራማሪ ‹‹በነዳጅ ድጎማው መነሳት የበለጠ ተጎጂ የሚሆነው ማኅበረሰቡ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ነዳጅ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ መምረጥ ስለሚጀምር ከአካባቢ አንፃር ጥሩ ነው፡፡ ያረጁ መኪኖችን ማስመጣትም ይቆማል፤›› ይላሉ፡፡

‹‹የዋጋ ንረት ከአሁኑ ጣሪያ እየነካ ሲሆን የጦርነቱ ዳፋም አላለቀም፡፡ ከአማራ ክልል የሚመጣ ምርት በሁለት ሦስተኛ ቀንሷል ከሌሎች አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ምርትም መቀነሱ ተደማምሮ ኑሮን ከአቅም በላይ ሊያደርግ ይችላል፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

የነዳጅ አከፋፋዮች ብሶት

ለረዥም ዓመታት ነዳጅ አከፋፋዮች የትርፍ ህዳጋችን የቀጨጨ ነው በማለት ሲያማርሩ የቆዩ ሲሆን፣ አዲስ የወጣው መመርያ ይኼንንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ትክክለኛ ቦታው ለማምጣት አልሟል፡፡ ‹‹ አጂፕና ሼል ከዚህ አገር የወጡት የትርፍ ህዳጉ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በታች ስለሆነ ነው፡፡ እኛም ከመንግሥት እኩል ድጎማውን ተሽክመን ነው የኖርነው፡፡ በነዳጅ ማከፋፈል ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ወደ ነዳጅ ኮንትሮባንድ የሚገቡት የትርፍ ህዳጉ በቂ ስላልሆነ ነው፤›› የሚሉት በኢትዮጵያ የነዳጅ ማደያዎች ማኅበር የቦርድ አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ናቸው፡፡

አንድ የነዳጅ ቦቴ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ 80 ሺሕ ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ ማደያዎች ከአንድ ቦቴ አሥር ሺሕ ብር ብቻ እያተረፉ መቀጠል አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከተሞች አካባቢ በቀን ብዙ ቦቴ መሸጥ ይቻላል ግን ወጣ ያሉ አካባቢዎች በወር አንድ ቦቴ እየሸጡ ትርፍ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ነፃ ገበያ ቢባልም በተግባር ግን ዘርፉ በዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ነበር፤›› ይላሉ አቶ ኤፍሬም፡፡

አዲሱ መመርያ ለነዳጅ አጓጓዥ ድርጅቶች ለአከፋፋዮችና ለማደያዎች አዲስ ስሌት ያወጣ ሲሆን፣ በየወሩ ከፍ እየተደረገ የትርፍ ኅዳጉን ክፍተት ለመሙላት ታቅዷል፡፡

ይሁን እንጂ ማኅበራቱ አሁንም ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ አዲሱ መመርያ ‹‹የትርፍ ህዳግ የሚሰላው በወቅቱ ባለው የባንክ ወለድ ምጣኔ ላይ ከሰባት እስከ አሥር በመቶ በመጨመር ይሆናል፤›› ይላል፡፡

ማኅበራቱ ግን መንግሥት የሚባክነውን ነዳጅ በአግባቡ ከግምት አላስገባም ይላሉ፡፡ ‹‹ሦስት እጅ የሚሆነው ነዳጅ በትነት ይጠፋል፡፡ ከመንግሥት የምንቀበለውና መጨረሻ ላይ የምንሸጠው የነዳጅ መጠን በትነት ይቀንሳል፤›› ብለዋል አቶ ኤፍሬም፡፡

በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ ግን አዲሶቹ መመርያዎች በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ ወሳኝ ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹ዘርፉ በነፃ ገበያና በውድድር ብቻ የሚመራበትን ሥርዓት እያበጀን ነው፡፡ ትርፋማ ለመሆን የነዳጅ ድርጅቶቹ ከትርፍ ህዳግ በተጨማሪ የጎን ቢዝነሶችን በጥራት ማቅረብ አለባቸው፤›› ይላሉ አቶ ታደሰ፡፡

በአገሪቱ በ1,200 ማደያዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ በኦሮሚያ 390፣ አማራ 260፣ ደቡብ 170 እና አዲስ አበባ 150 አላቸው፡፡ በመሬት ዋጋ መወደድ ምክንያት አንድ ማደያ ለመክፈት እስከ 40 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉ ደግሞ ፈተና ሆኗል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ነዳጅ በዱቤ መስጠት ማቆሙም አዳዲስ ድርጅቶች ወደ ዘርፉ እንዳይቀላቀሉ አድርጓል፡፡

‹‹በፊት አንዳንድ አዳዲስና በቂ ካፒታል የሌላቸው የነዳጅ ድርጅቶች በዱቤ ወስደው በጥቁር ገበያም ነዳጁን ሸጠው ዕዳቸውን ይመልሱ ነበር፡፡ አሁን ዱቤ በመቆሙ በዘርፉ ውስጥ አዳዲስ ድርጅቶች መግባት አልቻሉም፡፡ የነዳጅ ዘርፍ ብዙ ካፒታል ቢፈጅም ከማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ የቢዝነስ ዘርፍ ጋር ሲወዳደር ትርፉ የወረደ ነው፤›› ይላሉ አቶ ኤፍሬም፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት በነዳጅ ላይ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ከተጋረጠበት የገንዘብ እጥረት አንፃር ተገቢ ቢመስልም፣ ወቅቱን ያልጠበቀና ተፅዕኖውም ከወትሮው የዋጋ ጭማሪ የገዘፈ እንደሚሆን ምሁራን ይስማማሉ፡፡   

Published on 30 Jan-2022 አሸናፊ እንዳለ - ሪፖርተር ቢዝነስ 

Related Post