ecx coffee


የአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ በመሆን በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቡና በኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን ገቢ ያገኘበት ወቅት መሆኑ ሲገለጥ፣ በአንፃሩ የኢትዮጵያ የቡና ግብይት ላይ ብዥታ የተፈጠረበት ሆኗል፡፡

ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ ከ578 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘውም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያሳየ ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ በግማሽ ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የተገኘበት ትልቁ እንደሆነም መረጃው ያመለክታል፡፡

እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ፣ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 148,882 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ ለተለያዩ አገሮች ተሸጧል፡፡ ይህ ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር በ57 ሺሕ ቶን ብልጫ ያለው ነው፡፡

የቡና የወጪ ንግድ እስካሁን በግማሽ ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘበት ጊዜ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከ25 በመቶ እስከ 30 በመቶውን የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከቡና ወጪ ንግድ ቢሆንም፣ በየዓመቱ ከምርቱ ይገኛል ተብሎ የሚያዙ ዕቅዶች ሙሉ ለሙሉ አለመሳካታቸውም የሚገለጽ ነበር፡፡

በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ግን ከታቀደው ጋር ተስተካካይ የሆነ ገቢ መገኘቱን የሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር እየሄደ ነው፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የቡና ወጪ ንግድ የተወሰኑ መሻሻሎች እየታዩበት ቢሆንም፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ ይህንን ዕቅድ ማሳካት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ዘንድሮ ግን ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምናልባትም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሻገር ይችላል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተገኘው የወጪ ንግድ ግኝትም ጠቋሚ እንደሚሆን ታምኗል፡፡

ዘንድሮ በስድስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው ውጤት ምናልባትም በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት እንዲሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ከቡና ወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

የስድስት ወራት የቡና ወጪ ንግድ ገቢ ማደግ ዘንድሮ የታየው የዓለም ቡና ዋጋ በመጨመሩ ነው የሚል አመለካከት ስላለ ይህስ አስተዋጽኦ አላደረገም ወይ ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹በዓለም ገበያ የተወሰነ የዋጋ ለውጥ አለ፡፡ እሱም አንድ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን የሪፎርም ሥራው ትልቅ ለውጥ ማምጣቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

በመንግሥት ዕቅድ መሠረት በ2014 ዓ.ም. በሙሉ በጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ለማግኘት የታቀደው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የዚህን ያህል የውጭ ምንዛሪ ቡና ሊያስገኝ ከቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ እያደገ መምጣትና የብራዚልና የኮሎቢያ ቡና በውርጭ መመታት ነው፡፡ የባለሥልጣኑ መረጃ ደግሞ፣ ከቡና ምርት ጋር በተያያዘ በተሠራው ሪፎርም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የቡና ምርት እየጨመረ መምጣቱንም አንድ ምክንያት እንደሆነ ያመለክታል፡፡

ከቨርቲካል ኢንቲግሬሽን ጋር ተያይዞ ማሻሻያዎች ከተደረጉ በኋላ ብዙ ለውጦች እያመጡ ነው ያሉት አቶ ሳህለማርያም፣ ሪፎርሙ የቡና የወጪ ንግድን እንዴት ሊያሳድገው ቻለ? ምን ስለተደረገ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያም፣ ‹‹ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ ነበር ግብይት የሚፈጸመው፡፡ አሁን የተለያዩ አማራጮ ተፈጥረዋልና እነዚህ የገበያ አማራጮች ጥቅም አስገኝተዋል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ሪፎርም መሠረት አርሶ አደሩንም በተወሰነ መልኩ ተጠቃሚ እያደረጉት ስለሆነ ምርቱን ቶሎ ቶሎ እያወጣ እንዲሸጥ አስችሏል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል በኮንትሮባንክ የሚወጣው ቡና አሁን ላይ አርሶ አደሩም ሆነ ሌላውም ተዋንያን የተሻለ ገቢ ስላገኘበት ወደዚህ ሥርዓት እየገባ በመምጣቱ ውጤቱ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ከሰሞኑ ከቡና ግብይት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ብዥታ አሁን የተገኘውን ዕድል በአግባቡ እንዳንጠቀም እንዳያደርገን መጠንቀቅ አለብን ይላሉ፡፡

በአገር ውስጥ የተሠራው ሪፎርምም ሆነ የዓለም የቡና ዋጋ መጨመርና እንደ ብራዚል ያሉ ዋነኛ ቡና ላኪ አገሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በገበያቸው ላይ የገጠማቸው ክፍተት ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ በቀጣይ ወራትም የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል የሚል ትንበያ አለ፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ቡና አምራቾችና ማኅበራት የቡና ምርታቸውን ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ አታቅርቡ ብለዋል ብለው አንዳንድ የቡና አቅራቢዎች እየወሰዱ ያሉት ዕርምጃ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡

በዚህ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገበሬዎችንና ማኅበራትን ቡና  እየዘረፈ በመሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቀጥታ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ያቅርቡ የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡ ይህንንም ንግግር ተከትሎ ባለፈው ሳምንትና በአሁኑ ሳምንት ቡናቸውን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚገበያዩ አቅራቢዎች ወደ ምርት ገበያ የሚልኩትን ቡና ቀንሰዋል፡፡

አቶ ሽመልስ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የተናገሩት ይህ ንግግር በአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚቀርበው ቡና እንዲቀንስ አድርጎታል ተብሏል፡፡ ከክልሉ አንዳንድ አቅራቢዎች ወደ ምርት ገበያው የሚያስገቡትን ቡና ያቆሙ ሲሆን፣ ይህም ምርት ገበያው የሚገበያየውን የቡና ምርት መጠን እየቀነሰው መሆኑ ታውቋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ይቀርብ የነበረው ቡና ወደ ምርት ገበያው አለመግባቱ አጠቃላይ የቡና ግብይት ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋትም አሳድሯል፡፡

አሁንም ምርት ገበያው ከሌሎች ክልሎች የሚመጣውን ቡና እያገበያየ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ክልል ወደ ምርት ገበያው የሚመጣው መቀነሱን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

ሆኖም የምርት ገበያው በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በፌዴራል ደረጃ የወጣውን አሠራር እንዲህ ባለው መልኩ መበረዙ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል የሚሠጉ ወገኖች፣ ግብይቱ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ እንዳይጓዝ እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ፡፡

በአንዳንድ ወገኖች ደግሞ ምርት ገበያው ብዙ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ቡና ከምርት ገበያው ወጥቶ በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ መፈጠር ያለበት ስለመሆኑ ቢያመለክቱም፣ ግብይቱን በምርት ገበያው በኩል አለማድረግ ለባሱ ችግሮች ሊያጋልጥ እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡

 በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና የወጪ ንግድ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ 907 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም 248,311 ቶን ቡና በመላክ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ አፈጻጸሙ በመጠን 80 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ 77 በመቶ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ታሪክ ተለውጦ ከቡና ወጪ ንግድ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ይገኛል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

ለዚህም ደግሞ የብሔራዊ ባንክ በቅርብ የወጣ መመርያ አጋዥ ይሆናል፡፡ ከወቅታዊው የዓለም የቡና ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዚህ አጋጣሚ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን በቅርብ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባልተለመደ መልኩ ለቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ባንኮች ብድር እንዲሰጡ ውሳኔ ላይ መድረሱ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ የወሰነው ይህ ውሳኔ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚገኘው የመጠባበቂያ ገንዘባቸው ላይ ሁለት በመቶውን በመውሰድ ለቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ብድር ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ዕድሉን ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡

Published on 26 January 2022 ዳዊት ታዬ - ሪፖርተር ቢዝነስ 

Related Post